በመንግስት ልማት ድርጅቶች የፋይናንስ መዝገብ ሥርዓትን በሚመለከት ለድርጅቱ የስራ መሪዎች ስልጠና ተሰጠ

Body: 

በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በዋናው መ/ቤት ለሚገኙ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የመምሪያው ዳይሬክተሮች፣ የፋይናንስና አካውንትስ መምሪያ የሥራ መሪዎች እንዲሁም ለቃሊቲ፣ ለገላንና ለሞጆ ወደብና ተርሚናል ቅ/ጽ/ቤት የሥራ መሪዎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ መዝገብ ሥርዓትን (IFRS) የሚመለከት ለሁለት ቀናት የቆየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከታህሳስ 07 – 08/2010 ዓ/ም ተሰጥቷል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህራን ሲሆኑ የስልጠናውን ዋና ዓላማ አቶ አባት አበበ ሲገልጹ በመንግስት ሥር የሚገኙ ድርጅቶች ወጥ የሆነና በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓትን ለመዘርጋት፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ለመደገፍ፣ የፋይናንስ ቀውስና የድርጅቶችን ውድቀት ስጋት እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸውን አሉታዊ የኢኮኖሚ ውጤቶች ለመቀነስ እና ከድርጅቶች የሚገኘውን የፋይናንስ መረጃ አቅርቦት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህ አሰራርም በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቁጥር 847/2006 መሰረት ወጥቶ እስከ 2010 ዓ/ም የበጀት ዓመት መጨረሻ በትልልቅ የመንግስት እና የግል ድርጅቶች ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን ያስታወሱት አቶ አባት በአሁኑ ሰዓት ግን በአገራችን እየተሰራበት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ በዘልማድ የሚሰራና የግብር አዋጁ ያስቀመጠውን ግዴታ ለመወጣት ያለመ ብቻ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ አዲሱ የፋይናንስ መዝገብ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውና የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ጨምሮ ከታዳጊ እስከ የበለጸጉ አገራት የሚጠቀሙበት አሰራር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ እንደ ኢባትሎአድ የመሳሰሉ ድርጅቶችም የፋይናንስ አሰራራቸውን በዓለም አቀፉ የፋይናንስ መዝገብ ሥርዓት መሰረት መስራታቸው ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የሚኖራቸውን የብድርም ሆነ ሌሎች የፋይናንስ ግንኙነቶች የተሳካ ከማድረጉም በላይ ቀላል፣ ጤናማ፣ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ለመገንባት እንደሚያስችል ጨምረው ገልጸዋል፡፡