ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

Body: 

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በዘርፉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት እና የዕውቀት ሽግግር ማድረግ የሚያስችል የጋራ ስምምነት ሰነድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የካቲት 24 ቀን 20009 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡
በስምምነት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕ/ር አድማሱ ጸጋየ እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደሴት ሆነው ከመቀመጥ ይልቅ ከኢንዱስትሪዎችና ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመስራትና ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ መስኮች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ፕ/ር አድማሱ ጸጋየ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መፈራረሙ ያለውን ጠቀሜታ ሲገልጹ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ እንደመሆኑ መጠን ካለው የመማርና ማስተማር ልምድ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ያካበተውን ልምድ በማቀናጀት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ከአሁን በፊት በአፍሪካ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወዳድሮ በአራት መስኮች ማለትም በባቡር፣ በጤና፣ በባዮ ዳይቨርሲቲ ቲቺንግ እና በውኃ ማኔጅመንት ላይ የአፍሪካ ልህቀት ማዕከል በመሆን ለመስራት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በኩል የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት የድርጅቱ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ ሲሆኑ ድርጅቱ በባሕር ትራንስፖርት፣ በጭነት አስተላላፊነት እና በወደብና ተርሚናል ዘርፍ ተሰማርቶ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
አቶ መስፍን አያይዘው ሲያስረዱም የማሪታይምና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍን ለማዘመንና ብቁና ተወዳዳሪ አገልግሎት ለመስጠት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የሰው ኃይል ልማት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱም ይህን መሠረት በማድረግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በአራት ጉዳዮች ላይ ተባብሮ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ እንደተፈራረመ ገልጸው በዋናነትም ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ስልጠና ለማግኘት፣ በዘርፉ የማስተርስ ፕሮግራም ለማስጀመር፣ የባቦጋያን ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ ድጋፍ ሊያደርግ የሚያስችል እና ችግር ፈች የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ዓላማ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
እስካሁንም ድርጅቱ በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት ባለሙያዎችን ጋና እና ሌሎች አገራት ድረስ በመላክ እንዲሰለጥኑ የሚያደርግ ሲሆን በዚህም ድርጅቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ እያወጣ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ግን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በድርጅቱ የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ በባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ ማለትም Deck, Engine, Engine Service, Freight Forwarding, Port and Terminal ዲፓርትመንቶች ከደረጃ 1-5 ባሉ የቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ እና በቀጣይ ዓመት ሥልጠና እንደሚጀምር የድርጅቱ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ ጨምረው ገልጸዋል።