የድርጅቱ የሥራ መሪዎች ጉባዔ ተካሄደ

Body: 

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሥራ መሪዎች ጉባዔ በአዳማ ከተማ ከጥር 20-21/2009 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ በጉባዔው ላይ የዋናው መ/ቤት እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ስራ መሪዎች የተገኙ ሲሆን የድርጅቱን የ2009 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ስድስት ወራት የመደበኛ ሥራ፣ የካፒታል ፕሮጀክት፣ የለውጥ እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል፡፡

የድርጅቱ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ ያለፈውን ስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በዝግጅት ምዕራፍ በኩል የተከናወኑ ተግባራትን ሲገልጹ ከስትራቴጂክ ዕቅድ በመነሳት የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ በውጤት ተኮር ስርዓት መሰረት በማዘጋጀት እና ከሁሉም ሰራተኞች ጋር የጋራ ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን አውስተው በዕቅድ ከተያዙት ተግባራት ውስጥ አብዛኞቹ መፈጸማቸውን በሪፖርቱ ገልጸዋል፡፡ በተለይም የድርጅቱን አገልግሎት ከማስፋፋት፣ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ከማድረግ እንዲሁም የማስፈጸም አቅም ከመገንባት አንጻር በርካታ ስራዎች እንደተከናወኑ በሪፖርቱ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

የድርጅቱ ከፍተኛ የስራ መሪዎች የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአዳማ

የድርጅቱን ዋና ዋና የመደበኛ ሥራዎችን ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸም በሚመለከት አቶ መስፍን ሲገልጹ የድርጅቱን መርከቦችና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም በባሕር ላይ 2,365,387 ቶን ገቢ ዕቃ ያጓጓዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በመልቲ ሞዳል ስርዓት 70,327 TEU ኮንቴይነር እና 5425 ተሽከርካሪዎች በባሕር ላይ አጓጉዟል ብለዋል፡፡
በጭነት ማስተላለፍ አገልግሎት ዘርፍ በባሕር ከተጓጓዘው ውስጥ 93,180 TEU እና 5,486 ተሽከርካሪዎችን በመልቲ ሞዳል የትራንስፖርት ስርዓት ወደ ሀገር ውስጥ ወደቦችና የጉምሩክ ፍቃድ ያላቸው መጋዘኖች (Bonded Warehouses) ሲያጓጉዝ በዩኒ ሞዳል ስርዓት አማካኝነት ደግሞ 1,210,604 ቶን ለሚሆን ገቢ ጭነት የማስተላለፍ አገልግሎት እንደተሰጠ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 116,468 ቶን ወጪ ጭነት ማስተላለፉን በሪፖርቱ አመላክተዋል፡፡
የወደብና ተርሚናል አገልግሎትን በተመለከተ በመልቲ ሞዳል ስርዓት ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው ጭነት ውስጥ ለ88,379 TEU ኮንቴይነር እና ለ4,912 ተሽከርካሪዎች የወደብ አገልግሎት እንደተሰጠ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡
በአጠቃላይ ድርጅቱ የባሕር ትራንስፖርት፣ ጭነት ማስተላለፍ እና የወደብ አገልግሎት በመስጠት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 8.138 ቢሊዮን ብር ማስገባት ችሏል ብለዋል፡፡
ከቀረበው ሪፖርት በመነሳት ከውይይቱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በተለይም ድርጅቱ የሚያስገነባቸው የተለያዩ የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መዘግየት፣ የግዥ ሥርዓቱ መጓተት፣ ከባለ ድርሻና አጋር አካላት ጋር ያለው የቅንጅትና የትብብር ስራዎች ማነስ፣ ከውስጥ ሰራተኞችና ከውጪ ደንበኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎች አፈታት በሚመለከት፣ ሰራተኛው የሚያነሳውን የማበረታቻና ማትጊያ ስትራቴጅዎች ተግባራዊ አለመደረግ፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት እና መልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው የሥራ መሪዎችና አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የቀጣይ ጊዜያት የድርጅቱ የአራቱም ዘርፎች የትኩረት አቅጣጫዎችና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በዝርዝር ቀርበው አስተያየት የተሰጠባቸው ሲሆን የድርጅቱን ሁለገብ የህንጻ ግንባታ፣ የሞጆ ወደብና ተርሚናል የማስፋፊያ ፕሮጀክት እና ወደብና ተርሚናሉን ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር የማገናኘት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲጠናቀቁ የክትትልና ድጋፍ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚን ግብዓት በማሟላት ቀጣይ ዓመት ስልጠና ለማስጀመር ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባ፣ በቀሪ ጊዜያት የታቀዱ የአገር ውስጥና የውጪ አገር ግዥዎች እንዲጠናቀቁ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን ማፋጠን፣ የኦፕሬሽኑ የመረጃ ቅብብሎሽ በተሟላ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ማድረግ፣ ተጠንቶ የቀረበው የደሞዝ ስኬል በአጭር ጊዜ ተግባራዊ የሚሆንበት ሁኔታ ላይ ድጋፍ መስጠት፣ በሂደት ላይ ያለው የሂሳብ መዝጋት ስራ በተፋጠነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ማድረግ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩ እንዲፈታ ማመቻቸት የሚሉት በቀጣይ የድርጅቱ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ በውይይቱ ተገልጿል፡፡