ድርጅቱ በማሪታይምና ሎጅስቲክስ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገለጸ

Body: 

በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ታህሳስ 14/2009 ዓ/ም ተመረቀ።

አካዳሚው በባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ አገራችን የምትፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል እንደሆነ የድርጅቱ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ ገልጸዋል። አካዳሚው በ2002 ዓ.ም ተገንብቶ ስራ ሲጀምር በዓለም አቀፉ የማሪታይም ህግና ደንብ፣ በSTCW 1978 ኮንቬንሽን እና በማኒላ 2010 አሜንድመንት መሰረት ድርጅቱ በሚያሰማራቸው መርከቦች ላይ ተመድበው የሚሰሩ ሁሉም የባህር ሰራተኞች ዓለም አቀፉ የማሪታይም ድርጅት ያስቀመጠውን አስገዳጅ የባህር ላይ ደህንነት ስልጠና ለመስጠት በማሰብ እንደሆነ አቶ መስፍን ተፈራ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት 8 ዓመታትም 2927 ለሚሆኑ የድርጅቱ የባህር ሰራተኞችና የግል ሰልጣኞች አጫጭር ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ግንባታ ሦስት ዓመታት የፈጀ ሲሆን ለግንባታው የወጣው 44 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ሙሉ በሙሉ በድርጅቱ ተሸፍኗል፡፡ አካዳሚው በነባሩ የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለአንድ ወር ብቻ ሲሰጥ ከቆየው መሰረታዊ የባህር ላይ ደህንነት ስልጠና በተጨማሪ በአምስት የተለያዩ ዘርፎች ከደረጃ 1-5 የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ እና በቀጣይ አካዳሚው ከአሁን በፊት በአንድ ጊዜ 48 ሰልጣኞችን ብቻ ተቀብሎ ሲያሰለጥን የነበረውን የቅበላ አቅም ወደ 168 ከፍ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ እና የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አህመድ ሺዴ እንደገለጹት መንግሥት የአገሪቱን የልማት እንቅስቃሴ ለማፋጠን የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን ላይ ትኩረት አድርጓል ብለዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የአካዳሚው እውን መሆን በሎጅስቲክስ ዘርፍ ያለው የሰው ኃይል አቅም ክፍተት በመሙላት በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ እንድትሰለፍ የገቢና ወጪ ንግዱን ሊያሳልጥ የሚችል የባሕር ትራስፖርት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል። ይህን ሊያሳልጥ የሚችል የማሪታይምና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ለመፍጠር ደግሞ ዘርፉን በማሳደግ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የሰው ኃይል ልማት መሆኑን ተናግረዋል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አካዳሚው የሚያስፈልገውን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ለማሟላት ከድርጅቱና ከአካዳሚው ጋር በጋራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። ''በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚከፈቱ የአቅም ግንባታ ስልጠና ማዕከላት ለአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ተቋማት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ጭምር መሆን ይገባቸዋል'' ብለዋል።

በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ወቅት ለአካዳሚው ግንባታ ማስፋፊያ ድጋፍ ላደረጉ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የዕውቅና ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረጉ ቃል ገብተዋል፡፡