የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን በአገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማና ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚሰራ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

Body: 

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ግርማ አመንቲ እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን እና በስሩ የሚገኙትን ባቦጋያ የባህረኞች ማሰልጠኛ ተቋም እንዲሁም ገላን እና ሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናልን ህዳር 3/2009 ዓ.ም ጎብኝተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናልን ሲጎበኙ
ክቡር ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት በድርጅቱ ላይ ህዝብና መንግስት የጣለበትን ትልቅ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣና በአገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የበኩሉን ሚና ይወጣልብለዋል፡፡
የድርጅቱን ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት ለማሳደግ ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ የማዘመንና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚሰሩ ገልጸው ድርጅቱ የአገሪቱን ገቢና ወጪ ዕቃዎች የሚያንቀሳቅስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እያከናወነ ያለው ስራ በጣም ሰፊና ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን ከዚህ አኳያ ስራውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል አገልግሎት ቅ/ጽ/ቤት 15 ሺህ ኮንቴይነሮችን የመያዝ አቅም እንዳለውና በአሁኑ ወቅትም በወደቡ 14 ሺ ኮንቴይነሮች እንደሚገኙና አጠቃላይ የአገሪቱ የወጪና ገቢ ዕቃዎች 78የሚሆነው በዚሁ ወደብ የሚስተናገዱ እንደሆነ የቅ/ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ታየ ጫላ ለሚኒስትሩና ለጎብኝዎች አብራርተዋል፡፡
24 ሰዓት ሙሉ አገልግሎት የሚሰጠው የደረቅ ወደብና ተርሚናል ቅ/ጽ/ቤቱ በቀን ከ2 ሺ 300 በላይ ኮንቴይነሮችን እያስተናገደ እንደሚገኝ አቶ ታየ ገልጸው ወደቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ለማሳደግ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኝና ወደቡን ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር ሃዲድ ጋር የማገናኘት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል
በተያያዘ የገላን ደረቅ ወደብና ተርሚናል በ21 ሄክታር መሬት ላይ እንዳረፈ፣ አንድ ሺ 700 መኪኖችን የመያዝ አቅም እንዳለውና በአሁኑ ጊዜም 7 መቶ 34 ተሸከርካሪዎችን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ ለክቡር ሚኒስትሩና ለጎብኝዎች ተጠቅሷል፡፡
ቢሾፍቱ የሚገኘውና በድርጅቱ ስር የሚገኘው ባቦጋያ የባህረኞች ማሰልጠኛ ተቋም ሌላው ጉብኝት የተደረገበት ሲሆን ባህረኞችንና የባህር ላይ ስራ ደህንነትን የተመለከቱ ስልጠናዎችን በመስጠትና ዓለም አቀፉ የማሪታይም ድርጅት ያስቀመጠውን አስገዳጅ የባህር ላይ ደህንነት ስልጠና በመስጠት ብቁ ተወዳዳሪና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎችን እያፈራ እንደሚገኝ ለክቡር ሚኒስትሩና ለጎብኝዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡