የ1ኛ ሩብ አመት የመደበኛ እና የለውጥና መልካም አስተዳደር ስራዎች አፈጻጸም

Body: 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በመጀመሪያው ሩብ አመት ከ1.2 ሚሊዮን ቶን በላይ እቃ ማጓጓዙ ተገለጸ፡፡ ከ4.1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱም ተጠቁሟል

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የ1ኛ ሩብ አመት የመደበኛ እና የለውጥና መልካም አስተዳደር ስራዎች አፈጻጸምን አስመልክቶ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የአራቱም ዘርፎች ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎች እና የሥራ መሪዎች በተገኙበት በሂልተን ሆቴል ጥቅምት 8-9/2009 ዓ.ም ገምግመዋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ አህመድ ቱሳ በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት ድርጅቱ በመጀመሪያው ሩብ አመት 1.2 ሚሊዮን ቶን በላይ ገቢ እቃ በድርጅቱና በኪራይ መርከቦች በባህር አጓጉዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከአንድ በላይ የትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም 30 ሺ ኮንቴነር እና ከ2 ሺ 4 መቶ በላይ ተሽከርካሪ በባህር ማጓጓዙን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ አያይዘው የገለጹት፡፡.
ድርጅቱ በጭነት ማስተላለፍ አገልግሎት ዘርፍም 50 ሺ የሚጠጋ ኮንቴነር እና 2 ሺ 3 መቶ የሚጠጋ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ዉስጥ ወደቦችና መጋዘኖች ማጓጓዙን ዋና ስራ አስፈጻሚው አመላክተዋል፡፡ አያይዘውም ድርጅቱ ከ55 ሺ ቶን በላይ ወጪ ጭነት ማስተላለፉን ጠቁመዋል፡፡.

ወደ ሀገር ዉስጥ ከገባው ጭነት ውስጥ 47 ሺህ ለሚጠጋ ኮንቴነር እና ከ2 ሺ በላይ ተሸከርካሪዎች የወደብ አገልግሎት መሰጠቱንም አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በሩብ አመቱ ውስጥ ለደንበኞች ከሰጠው የባህር ትራንስፖርት፣ ጭነት ማስተላለፍ እና የወደብ አገልግሎት ከ4.1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባቱንም ነው የገለጹት፡፡ ድርጅቱ ከታክስ በፊት 3 መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ትርፍ ለማግኘት አቅዶ ከእቅዱ በላይ ከ3 መቶ 25 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉም ተነግሯል፡፡.

ድርጅቱ እያስገነባቸው ያሉት ደረቅ ወደቦችና የዋና መስሪያ ቤት ሁለገብ ህንጻ መጓተቶች እንደሚስተዋልባቸው የተገመገመ ሲሆን ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም በውይይቱ ተሰምሮበታል፡፡
የድርጅቱን የጭነት ተሸከርካሪዎች እና መርከቦች ጭነት የማጓጓዝ አቅም ማጎልበት እንደሚገባም በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡
ከለውጥና መልካም አስተዳደር አኳያ የድርጅቱ የሎጂስቲክስ ሰራዊት ግንባታ መመሪያ፣ የ1ለ5 ቡድኖች፣ የህዝብ ክንፍ አደረጃጀት፣ ውጤት ተኮር እና አውቶሜሽን አፈጻጸም አስመልክቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የአገልግሎት አሰጣጥ እና የለውጥ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ መፈጸም እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

የድርጅቱ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ እንደዘገበው፡፡