የፌደራል የመንግስት መስሪያ ቤት የህዝብ ግንኙነት እና የሚዲያ አካላት በኢባትሎአድ የስራ ጉብኝት አደረጉ

Body: 

የፌደራል የመንግስት መስሪያ ቤት የህዝብ ግንኙነት እና የሚዲያ አካላት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የስራ እንቅስቃሴዎችን የተመለከተ የሁለት ቀናት የመስክ ጉብኝት ከየካቲት 16 – 17/2010 ዓ.ም ተደረገ፡፡
በዚህ የመስክ ጉብኝት ላይ በቃሊቲ ወደብና ተርሚናል እየተከናወነ ያለውን የኤክስፖርት ምርቶችን በሀገር ውስጥ አሽጎ የመላክ ሥራን፣ የገላን ወደብና ተርሚናልን የስራ እንቅስቃሴ፣ ቢሾፍቱ የሚገኘውን የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ እንዲሁም የሞጆ ወደብና ተርሚናል ከኢትዮ - ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር ተገናኝቶ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በተመለከተ በሚመለከታቸው የቅ/ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና በድርጅቱ የተለያዩ ኃላፊዎች ሰፊ ማብራሪያና ገለጻ ተሰጥቷል፡፡

የጉብኝቱ ዓላማ የአገራችን የወጪና ገቢ ዕቃዎችን በባህር ላይ በማጓጓዝ ቀልጣፋና ተደራሽ የሎጅስቲክስ አገልግሎት በመስጠት የአገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በከፍተኛ ደረጃ በማገዝ የማይተካ አስተዋጽኦ እያበረከተ ስላለው ኢባትሎአድ የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ አካላት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ እና እነዚህ አካላት ይህንን ተረድተው በዘርፉ እየተከናወኑ ስላሉት ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስ እንዲችሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በተለይም በቃሊቲ ወደብና ተርሚናል እየተከናወነ ያለው የኤክስፖርት ምርቶችን በሀገር ውስጥ አሽጎ የመላክ ሥራ ላኪዎች በውጭ ምንዛሪ የሚከፍሉትን ከፍተኛ ወጭ ከማስቀረቱ ባሻገር አላስፈላጊ ጊዜን እና እንግልትን የሚያስቀር እንደሆነ እና ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መሆን እንደቻለ ጭምር በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በገላን ተርሚናል እየተከናወነ ስላለው የገቢ ተሽከርካሪዎች የደረቅ ወደብ አገልግሎት፣ በድርጅቱ የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ በባህር ላይ የሚሰሩ ባህረኞችን በዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት (IMO) የትምህርት ስታንዳርድ መሰረት ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማብቃት ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ የሞጆ ወደብና ተርሚናልን የሎጅስቲክስ መናኽሪያ ለማድረግ እየተከናወኑ ስላሉት የገቢና የወጪ እቃዎች የመልቲሞዳል እና የዩኒሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓትና ወደብና ተርሚናሉ ከኢትዮ - ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር በማገናኘት እየሰጠ ስላለው አገልግሎት እና የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ለጎብኝዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም በተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በካፒቴን ተፈራ በዳሳ የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ እንዲሁም በአቶ ደሳለኝ ጉቱ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ተጠ/ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አማካኝነት ተገቢው ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡