ድርጅቱ ከሠራተኛ ማህበር ጋር የመግባቢያ ህብረት ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

Body: 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እና የድርጅቱ ሠራተኛ ማህበር የድርጅቱንና የሠራተኛውን ጥቅምና መብት ሊያስጠብቅ የሚያስችል የጋራ ስምምነት ሰነድ የድርጅቱ እና የማህበሩ ተወካዮች በተገኙበት የካቲት 15/2010ዓ.ም ተፈራረመ፡፡

ከድርጅቱ ሠራተኛ ማህበር ጋር የተፈራረሙት የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ሲሆኑ፡ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የሠራተኛው ስኬት ከድርጅቱ ዓላማ ስኬት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ እንደ አስተዳደርም እንደ ሠራተኛም ያለብን ኃላፊነት ሠፊ ነው ብለዋል፡፡

ይህ ሠፊ ኃላፊነት ደግሞ ድርጅቱ በዋናነት በህግ ተለክቶ ከተሰጠው ኃላፊነት በተጨማሪ በአገራዊ እንቅስቃሴም ካለው ድርሻ አንጻር ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎችን እና ብዙ ተስፋዎችን ሰንቀን ወደ ስኬት መሄድ ይገባናል በማለት ገልጸዋል፡፡

አቶ ሮባ አያይዘው እንደገለጹት ድርጅቱ መንግስት የሰጠውን ኃላፊነት እና የመፈጸም አቅም እንዲሁም የሠራተኛውን ምህዳር እና አደረጃጀቱን በማስፋት ለህብረተሰቡ የሎጅስቲክስን ምንነት ከማስረጽ ጀምሮ የሚፈለገውን የሎጅስቲክስ ትራንስፖርት አገልግሎት በተሟላ መልኩ እየሰጡ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ይህንን ኃላፊነት ለማሳካት ደግሞ ቁልፍ ሚና ያለው ሠራተኛውጋ በመሆኑ ሠራተኛው ባበረከተው አስተዋፅዖ ልክ የሚጠይቀውን መብትና ጥቅሙን የማስከበር ኃላፊነት የማኔጅመንቱ ድርሻ እንደሆነና በህብረት ስምምነቱ ችግር አለባቸው በተባሉ እና በተወሰነ መልኩ አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሠራተኛ ማህበሩ ጥያቄዎች መስተናገዳቸውን ጠቁመው፣ የተጀመሩ ስራዎችን ለማስቀጠል ሁላችንም ተግተን መስራት ይገባናል ብለዋል፡፡

የድርጅቱ ሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሠሎሞን አበራ በበኩላቸው ለኢንዱስትሪው ሠላም እና ህብረት ስምምነት ለመደራደር በጎ ህሊና እና ቅን አመለካከት እንደሚያፈልግና ለዚህም አሁን ያለውን አመራር አመስግነዋል፡፡ አያይዘውም ድርጅቱ ካለበት የገቢ መቀነስ አንጻር ሠራተኛ ማህበሩ ድርሻ በመውሰድ በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ማሻሻያ መደረጉን አመላክተዋል፡፡ ህብረት ስምምነቱ በስራ መደራረብ ምክንያት ከተባለለት ጊዜ የዘገየ ቢሆንም ከየካቲት 15 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንና ለሦስት ዓመት እንደሚፀና ገልጸዋል፡፡
የድርጅቱ እና የሠራተኛ ማህበሩ ተወካዮች በበኩላቸው የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትጋት በመወጣት በመልካም ሥነ ምግባርና ፍትሓዊ በሆነ መንገድ የድርጅቱን ምርታማነት ለማሳደግ እና የሠራተኛውን ጥቅም ለማስከበር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

File: 
File1: