የመጀመሪያው የካይዘን ትግበራ የዝግጅት ምዕራፍ ተጀመረ

Body: 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የለውጥ ሥራ አመራር መምሪያ ከኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለ209 ሠራተኞችና የስራ አመራር አባላት ከህዳር 12 እስከ 27/2010 ዓ.ም ድረስ መሰረታዊ የካይዘን ፍልስፍና ስልጠና በመስጠት ጥር 17/2010 ዓ.ም በቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የድርጅቱ የስራ አመራር አባላትና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች በተገኙበት የመጀመሪያውን የካይዘን ትግበራ የዝግጅት ምዕራፍ በይፋ ጀምሯል፡፡

አቶ ኃ/ስላሴ ግርማይ የለውጥ ሥራ አመራር መምሪያ ዳይሬክተር በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት ካይዘን የለውጥ መሳሪያ እንደሆነና ይህንን የለውጥ መሳሪያ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስፈልገው ግዙፍ ጉልበትና ዕውቀት ሳይሆን ለለውጥ ዝግጁ መሆንና ቀና አመለካከት እንደሆነ በመግለጽ ይህ የካይዘን ትግበራ እንደ መነሻ በቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተጀመረ ሲሆን በቀጣይ ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት እና በሌሎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ለማስተግበር የታቀደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ልንገረው አለማየሁ በቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የካይዘን ቢሮ አስተባባሪ ለፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ባደረጉት ገለጻ ከስልጠናው በኋላ በተሰሩ ስራዎች የአሰራርና የብክነት ችግሮች መኖራቸው ተለይተው የታወቁ ሲሆን በቀጣይ ችግሮቹን ለመቅረፍ ዕቅድ አዘጋጅተው ወደ ትግበራ በመግባት ችግሮችን እንደሚቀርፉ አብራርተዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት የካይዘን ተባባሪ አማካሪ አቶ ይበልጣል አስረሴ በበኩላቸው በዚህ በአጭር ስልጠና አመርቂ የሆነ ውጤት ማምጣት ስለማይቻል ድርጅታቸው ስልጠና በመስጠትና ትግበራውን በማስጀመር ብቻ የሚገታ ሳይሆን ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር ባደረገው የውል ስምምነት መሠረት የካይዘን ትግበራው ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ በየሁለት ሳምንቱ አፈጻጸሙን በመገምገም ድጋፍ የመስጠት እና የተለያዩ የማነቃቂያ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል

ተሳታፊዎች በበኩላቸው የወሰዱትን ስልጠና ወደ ተግባር በመቀየር የድርጅቱን ግቦች በላቀ ደረጃ ለመፈጸም እና የድርጅቱን ራዕይ ለማሳካት እጅ ለእጅ ተያይዘው ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡
በመጨረሻም ተሳታፊዎች ለካይዘን ትግበራው የተዘጋጁ የስራ ክፍሎችን በማጽደት የመጀመሪያውን የካይዘን ትግበራ የዝግጅት ምዕራፍ ስራ አከናውነዋል፡፡

File: 
File1: