12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዓመታዊ በዓል በኢባትሎአድ ተከበረ

Body: 

በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዓመታዊ በዓል የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ፣ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች እና የዋናው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የሚዲያ አካላ በተገኙበት ህዳር 23 ቀን በራስ ሆቴል ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ "በህገመንግስታችን የደመቀ ህብረ-ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሑፍ የቀረበ ሲሆን የድረጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ አስመልክተው ንግግር አድርገዋል በንግግራቸውም "የአገራችን የልማት የዲሞክራሲና የሰላም ግስጋሴ መሠረት ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የዕኩልነት እና ህገ መንግስታዊ ቃል ኪዳን ወደ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባታ የገቡበት ምዕራፍ ነው" ብለዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ አቶ ሮባ መገርሳ ሲናገሩ የፌደራሊዝም ስርዓት ብዙ ያደጉ አገሮች የመረጡት እንደሆነና በቋንቋ በባህልና በመልክዓ-ምድር የተለያዩ ህዝቦች በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ ልዩነታቸውን ለአንድነታቸው መሠረት አድርገው ያሳደጉት ስርዓት እነደሆነ የስዊዘርላንድ ተሞክሮ በማጣቀስ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ ይህ ስርዓት በአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ግን የቋንቋ የድንበርና የባህል የኋላቀርነት ተግዳሮቶች ያሉበት በመሆኑ የፌዴራል ስርዓቱን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ብዙ ጥረት መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ አቶ ሮባ መገርሳ ከእነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥ ዋናዋናዎቹን ጠቅሰው ሲያስረዱም የትምክህተኝት፣የጠባብነትና የጽንፈኝነት ተግዳሮቶች አንቀሳቃሽ የሆኑትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልሂቃን ዓላማ ጠንቅቆ ማወቅና ለብዙሃኑ ተጠቃሚነት መታገል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የፌደራሊዝም ስርዓቱ መሳካት ህዝቦች ፈቅደው የተስማሙበት ህገመንግስት የአገሪቱን ህገ መንግስት ታሪክ የለወጠ አዲስና የተሻለ የቃል ኪዳን ሰነድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የሚከበረው ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ህገመንግስታዊ መብት የተረጋገጠበት ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ህብረ-ብሄራዊ አገር ለመገንባት አበረታች ጥረቶች ውጤት ያሳዩበት በአገሪቱ በተፈጠረው አዲስ ህገመንግስታዊ ስርዓት አማካኝነት የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ምላሽ ያገኘበት እንደሆነ በዕለቱ በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡
የ12ኛው የብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ትርጉም የሚኖረው ሠራተኛው ውጤትን ማዕከል አድርጎ ለተጨማሪ ድሎች ሲንቀሳቀስ እንደሆነ እና በተለይ ወጣቱ ትውልድ ስራው ላይ ትኩረት ሰጥቶ የተጋ እንደሆነ ነው ያሉት አቶ ሮባ መገርሳ ድርጅቱ ያሉበት ተግዳሮቶች ብዙ በመሆናቸው ከሠራተኛው ቁርጠኝነት የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የተሳተፉ ሠራተኞች እና ከፍተኛ ስራ አመራር አባላት በዓሉን አስመልክቶ ያላቸውን አስተያየት የሰነዘሩ ሲሆን ዕለቱ ህዝቦች ለበለጠ ልማታዊ ትጋት እንዲነሳሱ አዲስ ምዕራፍ የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ በመስጠት በዕለቱ የቀረበውን የተሀድሶ ፕሮግራም እንዲከታተሉ የበዓሉን ታዳሚዎች በመጋበዝ በዓሉ በደመቀ ሁኔታ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ ዜማ በማቅረብ ተከብሮ ውሏል፡፡

File: 
File1: