በካንሰር ህመም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተካሄደ

Body: 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የስርዓተ-ፆታና ማህበራዊ ጉዳይ መመሪያ ከኢትዮጵያ የካንሰር አሶሲየሽን ጋር በመተባበር ለድርጀቱ ሴት ሰራተኞች በካንሰር ህመም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ህዳር 02/2010 ዓም በድርጀቱ መሰብሰያ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ የካንሰር አሶሲየሽን በ1994 ዓ.ም እንደተመሰረተና ዓላማውም ስለካንሰር ህብረተሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የካንሰር ታካሚዎችንና በሽተኞችን መንከባከብና መደገፍ፣ እንዲሁም ካንሰር በመንግስት በኩል ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ የመጎትጎትና የማስታወስ ስራ ዓላማ አድርጎ የተመሰረተ መሆኑን የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ በለጠ ገልጸዋል፡፡ ማህበሩ በተጓዘባቸው 16 ዓመታት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራውን በሬዲዮ፣ በጋዜጦችና በእንደዚህ አይነት መድረኮች ህብረተሰቡን ገጽ-ለገጽ በማግኘትና በዓለም አቀፍ የካንሰር ቀኖች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንደሚያከናውን ተገልጿል፡፡

በዕለቱም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱን የሰጡት የማህበሩ አባል ዶ/ር ቢኒያም ተፈራ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሀኪምና የመጨረሻ ዓመት የካንሰር ስፔሻሊስት ሲሆኑ በተለይ በሴቶች ላይ ብቻ በሚከሰቱ ሁለቱ የካንሰር አይቶች ማለትም የጡት ካንሰርና የማህጸን ጫፍ ካንሰር ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከአጠቃላይ የካንሰር አይነቶች 32 በመቶ የሚሆነውን የጡት ካንሰር የሚይዝ እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር ቢንያም የጡት ካንሰርን ሊያመጡ የሚችሉ ምክንያቶችን ብሎም የምርመራ ሂደቶችንና የህክምናውን ሁኔታ ለተሳታፊዎች በዝርዝር ገልጸዋል፡፡ ሌላኛው በሴቶች ላይ በብዛት እየተከሰተ ያለው የማህጸን በር ካንሰር ሲሆን ይህንንም ለመከላከል እድሜያቸው ከ15-49 ያሉ ሴቶች የቅድመ ካንሰር ምርመራ በሁሉም የጤና ተቋማት በነፃ መሰጠት ስለተጀመረ ምርመራውን ማድረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በካንሰር ህመም ዙሪያ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ልዩ ልዩ ጥያቄዎችና ስጋቶች የተነሱ ሲሆን ዶ/ር ቢኒያም ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የስርዓተ-ፆታና ማህበራዊ ጉዳይ አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ የንጉስነሽ አስራቴ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ብዙ ሴቶችን እያጠቃ የሚገኘውን የካንሰር ህመም ለመከላከል ሁሉም ሴቶች ወቅቱን የጠበቀ የቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚኖርባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ የካንሰር አሶሲየሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ በለጠ እንዳሉት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ለማግኘት ከተለያዩ ክፍለ ሀገራት የሚመጡና ማረፊያ ወይም መጠለያ በማጣት ህክምናውን እያቋረጡ ይመለሱ ለነበሩ ታካሚወች እንክብካቤና ድጋፍ የሚያደርግ ማዕከል በጉለሌ ከተቋቋመ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ እንደሆነና እስካሁን ቁጥራቸው 550 የሚሆኑ ታካሚዎች በዚህ ማህበር ድጋፍ እንደተደረገላቸው በመግለጽ የውይይቱ ተሳታፊዎችም የማህበሩ አባል በመሆን ወገኖቻቸውን እንዲደግፉና ማዕከሉን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

File: 
File1: