ድርጅቱ በ10ኛው ኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ መሳተፉ አገልግሎቱን በማስተዋወቅ ረገድ የጎላ ጠቀሜታ እንደነበረው ተገለጸ

Body: 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከጥቅምት 16 – 20 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል "የኢትዮጵያን ይግዙ" በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው 10ኛው ኢትዮ - ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ በመሳተፍ ለበርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ታዳሚዎች አገልግሎቱን አስተዋወቀ፡፡

የንግድ ትርዒቱ የኢፌዲሪ ንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር በቀለ ቡላዶ፣ ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የዲፕሎማሲ ተወካዮች እና የተሳታፊ ድርጅት ኃላፊዎች በተገኙበት ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም በድምቀት የተከፈተ ሲሆን በዕለቱም ለዕይታና ለንግድ የቀረቡ ምርትና አገልግሎቶች ተጎብኝተዋል፡፡

በዚህ የንግድ ትርዒት ላይ ኢባትሎአድን ጨምሮ የተለያዩ የአገር ውስጥ ድርጅቶች፣ ከዘጠኝ አገራት የመጡ ከ60 በላይ የንግድ ልዑካን ምርትና አገልግሎታቸውን በመያዝ ተካፋይ የነበሩ ሲሆን በየቀኑም በርካታ ሰዎች ጎብኝተውታል ፡፡ ኢባትሎአድ በዚህ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ተሳታፊ መሆኑ ድርጅቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለንግዱ ማህበረሰብ ከማስተዋወቁም ባሻገር አዳዲስ ደንበኞችን ለመሳብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው ተገልጿል፡፡
በዚህ የንግድ ትርዒት ላይ በመሳተፍ ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ሲያስተዋውቅ የነበረው ኢባትሎአድ በመረጃ አሰጣጥ፣ በተሻለ አቀራረብ፣ በተጠቀማቸው የተለያዩ የማስተዋዎቂያ ዘዴዎች (የህትመትና ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች) እና ባደረገው የስፖንሰር ድጋፍ ከሌሎች የሀገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች ጋር ተወዳድሮ የሁለት ዋንጫና በአጠቃላይ የ3ኛ ደረጃን በመያዝ 10ኛውን ኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በስኬት አጠናቅቋል፡፡
በቀጣይ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍና አገር ዓቀፍ መሰል የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ላይ ከዚህ በተሻለ ለማስተዋወቅ ትልቅ ልምድ የተወሰደበት እንደነበርም ታውቋል፡፡

File: 
File1: