የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ገለጹ፡፡

Body: 

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከድርጅቱ የሥራ አመራር አባላትና ከአጠቃላይ ሰራተኞች ጋር መስከረም 09/2010 ዓ/ም ውይይት አደረጉ፡፡

በውይይቱ ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንደተናገሩት ከጥልቅ ተሃድሶው ማግስት መንግስት የጸረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻን አጠናክሮ በማካሄድ የመንግስትንና የህዝብን ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ መጀመሩን አስታውሰው በቅርቡም የኢባትሎአድ ከፍተኛ አመራሮች በመንግሥት ኃብትና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው በህግ ጥላ ሥር እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ አክለውም መላው የድርጅቱ ሠራተኞች መደበኛ ሥራቸውን በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት ተረጋግተው ማከናወን እንዳለባቸው እና የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ሥራዎች በውክልና ተሰጥተው እንዲሰሩ መደረጉን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የኢፌዲሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠት በባህር ትራንስፖርት፣ በባቡር መስመር ዝርጋታ፣ በወደብና ተርሚናል አገልግሎት እና በመንገድ ግንባታ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የአገራችን የሎጅስቲክስ ዘርፍ ለማዘመን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱም በተፈጠረው ወቅታዊ ጉዳይ ክፍተት ሳይፈጠር የአገልግሎት አድማሱን በማስፋፋት በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የሎጅስቲክስ አገልግሎት በመስጠት አገራችን የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት ቁልፍ ሚና መጫወት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም የድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለድርጅቱ የሚሰጡትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

File: 
File1: