ዓመታዊ የድርጅቱ የሥራ መሪዎች ጉባዔ ተካሄደ

Body: 

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዓመታዊ የሥራ መሪዎች ጉባዔ በአዳማ ከተማ ከነሐሴ 06 - 07/2009 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ በጉባዔው ላይ የዋናው መ/ቤት እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ስራ መሪዎች የተገኙ ሲሆን የድርጅቱን የ2009 በጀት ዓመት የመደበኛ ሥራ፣ የካፒታል ፕሮጀክት፣ የለውጥ እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2010 ዕቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የድርጅቱ ፕላንና ዕቅድ መምሪያ ተወካይ አቶ ብርሃነ ገ/እግዚአብሔር በዝግጅት ምዕራፍ በኩል የተከናወኑትን ተግባራት ሲገልጹ ከስትራቴጂክ ዕቅድ በመነሳት የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ በውጤት ተኮር ስርዓት መሰረት በማዘጋጀት ከሁሉም ሰራተኞች እንዲሁም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የጋራ ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን አውስተው በዕቅድ ከተያዙት ተግባራት ውስጥ አብዛኞቹ መፈጸማቸውን በሪፖርቱ ገልጸዋል፡፡ በተለይም የድርጅቱን አገልግሎት ከማስፋፋት፣ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ከማድረግ እንዲሁም የማስፈጸም አቅም ከመገንባት አንጻር በርካታ ስራዎች እንደተከናወኑ በሪፖርቱ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

የድርጅቱን ዋና ዋና የመደበኛ ሥራዎች የ2009 በጀት አፈጻጸም በሚመለከት አቶ ብርሃነ ሲገልጹ የድርጅቱን እና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም በባሕር ላይ 5,319,286 ቶን ኮንቴይነር፣ ተሽከርካሪ፣ ጥቅል ዕቃ፣ ብረት እና ብትን ገቢ ዕቃዎችን ለማጓጓዝ ታቅዶ 4,538,722 ቶን ያጓጓዘ ሲሆን ይህም የዕቅዱን 85.3% መፈጸም ተችሏል ብለዋል፡፡
በጭነት ማስተላለፍ አገልግሎት ዘርፍ በባሕር ከተጓጓዘው ውስጥ በመልቲ ሞዳል ከጅቡቲ ወደ መሃል አገር 183,942 TEU ኮንቴይነር እና 21,961 ተሽከርካሪዎችን ለማጓጓዝ ታቅዶ 179,170 TEU ኮንቴይነር በማጓጓዝ የዕቅዱን 97% ማሳካት ሲቻል 9,464 ተሽከርካሪዎችን በማጓጓዝ የዕቅዱን 35.6% መፈጸም እንደተቻለ ገልጸው ተሽከርካሪ በማጓጓዝ ረገድ ዕቅዱ ዝቅ ያለበት ምክንያት በበጀት ዓመቱ ወደ አገር ውስጥ ከገቡት 48,862 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 68.7% ያህሉ በኮንቴይነር ታሽገው እና በዩኒ ሞዳል ስርዓት አማካይነት በመግባታቸው ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የትራንዚት ጊዜን 95% ለማድረስ በዕቅድ ከተቀመጠው 91% መፈጸም መቻሉን በሪፖርቱ አመላክተዋል፡፡
የወደብና ተርሚናል አገልግሎትን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ 174,744 TEU ገቢ ኮንቴይነር በወደቦች ለማስተናገድ ታቅዶ 169,241 ኮንቴይነር በማስተናገድ የእቅዱን 97% መፈጸም ሲቻል ወጪ ኮንቴይነር ደግሞ 169,131 TEU ለማስተናገድ ታቅዶ 171,346 ኮንቴይነር በማስተናገድ የእቅዱን 101% አሳክቷል፡፡
በአጠቃላይ ድርጅቱ የባሕር ትራንስፖርት፣ ጭነት ማስተላለፍ እና የወደብ አገልግሎት በመስጠት በበጀት ዓመቱ 15.811 ቢሊዮን ብር በማስገባት የዕቅዱን 82.08% ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የ2010 በጀት ዓመት የመደበኛ፣ የካፒታልና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ ቀርቧል፡፡

ከቀረበው ሪፖርት እና ዕቅድ በመነሳት ከውይይቱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በተለይም በበጀት ዓመቱ ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸውን የድርጅቱ መርከቦች አፈጻጸም፣ የወጪ ቅነሳ ስትራቴጅ አተገባበር፣ ድርጅቱ የሚያስገነባቸው የተለያዩ የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መዘግየት፣ የወደብ መሰረተ ልማቶች አለመሟላት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም በተለይም የድርጅቱ ICT አሰራር ደካማ መሆን፣ የገቢያ ማፈላለግ (የማርኬቲንግ) ሥራዎች በሚፈለገው ደረጃ አለመፈጸም፣ ከባለ ድርሻና አጋር አካላት ጋር ያለው የቅንጅትና የትብብር ስራዎች ማነስ፣ ከውስጥ ሰራተኞችና ከውጪ ደንበኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎች አፈታት በሚመለከት፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት እና መልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በሚመለከታቸው የሥራ መሪዎችና አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የቀጣይ ጊዜያት የድርጅቱ አቅጣጫዎችና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በሚመለከት አቶ ሮባ መገርሳ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚን በ2010 ዓ.ም ስልጠና ማስጀመር፣ የድርጅቱን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ አሰራር ማሻሻል፣ የወደብና ተርሚናል መሰረተ ልማትን ማሟላት፣ የተጀመሩ የተለያዩ የድርጅቱ ፕሮጀክቶች እና የመቐለ እና ኮምቦልቻ ወደቦችን ከባቡር መስመር ጋር የማገናኘት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲሰሩ የክትትልና ድጋፍ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ፣ የለውጥና መልካም አስተዳደር ሥራዎችን አመራሩ ትኩረት በመስጠት እንዲያስፈጽም፣ የድርጅቱን ፋይናንስ በሚመለከት የሂሳብ መዝጋት (ኦዲት) ሥራን ማጠናቀቅ እንደሚገባ እንዲሁም የብራንዲንግ እና ማርኬቲንግ ሥራዎች በቀጣይ ጊዜያት ተጠናክረው መሠራት አለባቸው የሚሉት በቀጣይ የድርጅቱ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ አቶ ሮባ ተናግረዋል፡፡

File: 
File1: 
File2: