ስልጠናው በአፈጻጸም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚረዳ ተገለጸ

Body: 

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ለዋናው ጽ/ቤት ሠራተኞች የጥልቅ ተሃድሶ ስልጠና ተሰጠ፡፡ ስልጠናው ለ593 የዋናው ጽ/ቤት ሠራተኞች ከሐምሌ 10 - 22/2009 ዓ.ም ድረስ በሁለት ዙር ተከፍሎ የተካሄደ ሲሆን የተሃድሶ መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ እንዲሁም የኢባትሎአድ ሚና በኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ በሚሉ ርዕሶች ላይ ያተኮረ እንደሆነ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ የድርጅቱ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚና የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ በስልጠናው መክፈቻ ወቅት ተናግረዋል፡፡

የስልጠናውን አስፈላጊነት አስመልክቶ አቶ ሲሳይ ሲያስረዱም ከአሁን ቀደም በተደራጀ አግባብ ለሁሉም ሰራተኞች እንዲህ ዓይነት ስልጠና ባለመሰጠቱ፣ በየደረጃው የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች በመኖራቸው እና አጠቃላይ በመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ስር ላሉ ሰራተኞች አቅም ለመገንባትና ለተልዕኮ የማብቃት ዓላማ አለው ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የአገራችንን ያለፉት አስራ አምስት ዓመታት ጉዞ ማየት በማስፈለጉና እንደ አገርም ያለንበትን አፈጻጸም በመገምገም በጥንካሬ የሚገለጹ ጉዳዮችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስኬድ እንዲሁም መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ቆም ብሎ ማስተካከል እንዲቻል የጥልቅ ተሃድሶው ስልጠና አስፈላጊ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የተሃድሶ መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ የሚለውን የመጀመሪያ ክፍል አቶ ደሳለኝ ገ/ህይወት የድርጅቱ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚና የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ያቀረቡ ሲሆን አገራችን ባለፉት ዓመታት ተከታታይነት ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን ጠቅሰው ነገር ግን የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች በመኖራቸው ምክንያት አሁንም ቢሆን የህብረተሰባችንን የልማት ተጠቃሚነትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት አገራችን ከድህነት ተላቃ የበለጸገ ህብረተሰብ የመገንባት፣ ከኋላቀርነትና ጸረ - ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ተላቃ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባትና በዚህ ጉዞ ውስጥ የህብረተሰባችንን መብትና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ፈተናዎች ውስጥ እንደምትገኝ አብራርተው እነዚህ ችግሮችን መፍታት የህልውናችን ጉዳይ እንደሆነ ጭምር አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም የኢባትሎአድ ሚና በኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ የሚለውን ሁለተኛ ክፍል አቶ ሮባ መገርሳ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያቀረቡ ሲሆን የአገራችን የባህር ትራንስፖርት አጀማመር በስልጣኔያችን በዓለም ቁንጮ በነበርንበት በአክሱም ዘመነ መንግስት እንደነበር አስታውሰው በዋናነትም ለገቢና ወጪ ንግድ እና ለወታደራዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ተናግረዋል፡፡
በዚህ መልኩ የተጀመረው የአገራችን የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት በርካታ ሂደቶችን በማለፍ በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የቆዩትን የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክሲዮን ማህበር፣ የባሕርና ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት፣ የደረቅ ወደብና ተርሚናል አገልግሎት ድርጅት እንዲሁም ኮሜት ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅትን በማዋሃድ በተማከለና ሁሉን አቀፍ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል በማሰብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 255/2004 መሠረት የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሚል ተቋቁሞ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ምንም እንኳ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ውጤቶችን በማስመዝገብ ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ቢሆንም የአገራችንን የሎጅስቲክስ ሥርዓት በማሻሻል፣ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ የትራንዚት ጊዜ እንዲኖር በማስቻል ረገድ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለዋል፡፡
በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በድርጅቱ የነበሩ ውስንነቶችን አቶ ሮባ ሲገልጹ በአመራሩ በኩል ስትራቴጂካዊ አመራር ያለመስጠት፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን መረጃ ሥርዓት ደካማ መሆን፣ የመልቲ - ሞዳል ሥርዓት በሚፈለገው መጠንና ዓይነት ማደግ አለመቻል እና ከዋጋና ቅልጥፍና አንጻር ተመራጭ አለመሆን፣ የመርከቦቻችን አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን፣ የፋይናንስ አስተዳደር ሥራዎች አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን፣ የግዥና አቅርቦት ሥራዎች እና የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ በቀረቡት ሰነዶች ላይ ሁሉም ሰራተኞች በቡድን በመሆን በሠፊው የተወያዩ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የሚመለከታቸው የሥራ መሪዎች ከመድረክ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ስልጠናውም በድርጅታችን የሚስተዋለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር እንዲሁም የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚረዳ የስልጠናው ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ ይህ ስልጠና ከዋናው ጽ/ቤት በተጨማሪ ለሁሉም ቅ/ጽ/ቤት ሰራተኞች እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

File1: