በሞጆ ደረቅ ወደብና በገላን የተሽከርካሪ ተርሚናል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሄደ

Body: 

በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሰራተኛ ማህበር አዘጋጅነት በሞጆ ደረቅ ወደብና በገላን የተሽከርካሪ ተርሚናል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሐምሌ 01/2009 ዓ.ም የማህበሩ ስራ አስፈፃሚዎችና የድርጀቱ ሰራተኞችን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

የኢባትሎአድ ሰራተኛ ማህበር ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን አበራ እንዳሉት የዚህ መርሃ ግብር ዓላማ ሀገሪቱ የተያያዘችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ እንዲሳካ ያለውን ድጋፍ ለመግለጽ ነው፡፡ የድርጅቱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በሚገኙበት አካባቢ ካሉ ማህበረሰቦች ጋር በመተጋገዝና ችግኞችን በማልማት የአካባቢ ስነ ምህዳር ሚዛን እንዲጠበቅ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ይህ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመከላከል ታሳቢ አድርጎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በዕለቱም በሞጆና ገላን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከ2500 /ሁለት ሺ አምስት መቶ/ በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የሰራተኛ ማህበሩ ስራ አስፈፃሚ እና የኦዲት ስራ አስፈፃሚ አባላት እንዲሁም የሞጆና የገላን የስራ መሪዎችና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በተለይ በሞጆ ደረቅ ወደብ ችግኞች መተከላቸው በበጋ ወቅት የሚከሰተውን ከፍተኛ ንፋስና አቧራ ለመከላከል የሚያስችል ከመሆኑም ባለፈ አካባቢውን ለምና አረንጓዴ በማድረግ በረሃማነትን እንዲቋቋም ያስችለዋል ተብሏል፡፡


እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን በቀጣይም ከድርጅቱ ጋር በመተባበር በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ማለትም በሃዋሳ፣ በመቀሌ፣ በኮምቦልቻ፣ በሰመራ እና በሌሎችም የክልል ከተሞች ችግኞችን ከማልማት ባለፈ ከየክልሉ መስተዳሮች ጋር በመነጋገርና የከተማ መንገድ በመውሰድ ለማልማትና የድርጅቱን አገልግሎት በቢል ቦርድ በፖስተርና በተለያዩ መንገዶች ለማስተዋወቅ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡

File: 
File1: