ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማህበር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

Body: 

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ሰነድ ከኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎች ማህበር ጋር ሰኔ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡

በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በኩል የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ሲሆኑ ድርጅቱ በባሕር ትራንስፖርት፣ በጭነት አስተላላፊነት እና በወደብና ተርሚናል ዘርፍ ተሰማርቶ ህዝብና መንግስት የጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሮባ አያይዘው ሲያስረዱም በአገራችን ያለው የሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ በተፈለገው መንገድ ያለማደግ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር አንዱ ምክንያት እንደሆነ አስታውሰው የሎጅስቲክስን ዘርፍ ለማዘመንና ብቁና ተወዳዳሪ አገልግሎት ለመስጠት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የሰው ኃይል ልማት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግም ድርጅቱ በባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ በባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ ማለትም Deck, Engine, Engine Service, Freight Forwarding, Port and Terminal ዲፓርትመንቶች ከደረጃ 1-5 ባሉ የቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ እና በቀጣይ ዓመት ሥልጠና እንደሚጀምር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሮባ መገርሳ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሳላሃዲን ከሊፋ በስምምነት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ማህበራቸው ላለፉት 20 ዓመታት በሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራ እንደሆነ ገልጸው ማህበሩ ከዓለም አቀፍ የጭነት አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማህበር በኩል በሚደረግ ድጋፍ በባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ የአሰልጣኞች ስልጠና በቀጣይ ወር መስጠት የሚያስችል ዓላማ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ከአሁን በፊትም ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ እንደተፈራረመ የሚታወስ ነው፡፡

File: 
File1: