የኢባትሎአድ ከፍተኛ የስራ መሪዎች ሰራተኞችና የድርጅቱ የመርከብ ወኪሎች/ኤጀንቶች/ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎበኙ

Body: 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከፍተኛ የስራ መሪዎች፣ ሰራተኞችንና የድርጅቱን የመርከብ ወኪሎች/ኤጀንቶች/ ያካተተ ቡድን ከሚያዝያ 20-22 2009 ዓ.ም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል፡፡

በቤንሻንጉል ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጉባ ወረዳ ሲርባ በተባለ ቦታ እየተገነባ ያለዉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት የሀይል መጠን የሚያመነጭ ሲሆን 246 ኪሜ ሰዉ ሰራሽ ዉኃ እንደሚፈጥርና በትልቅነቱም ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም ደግሞ 8ኛ ደረጃን እንደሚይዝ በጉብኝቱ ወቅት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ገልጸዋል፡፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ግብዓት የሚሆኑ ዕቃዎችን ከሚያጓጓዙ ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ተፈራ እንደገለጹት የግድቡ ግንባታ እንዲፋጠን ግበዓቶች በፍጥነት ተጓጉዘው የሚቀርቡበት አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡ ለግድቡ ግንባታ የሚመጡ በርካታ ትላልቅ የፕሮጀክቱን ገቢ እቃዎችን ተተርባይኖችን ጨምሮ ከመጫኛ ወደብ ጀምሮ ቅዲሚያ በመስጠትና በድርጅቱ መርከቦች በመጫን በዩኒሞዳል ትራንስፖርት ስርዓት ጅቡቲ ባለው ቅ/ጽ/ቤት የጭነት ማስተላለፍ ስራ ተጠናቆ በሚቀርቡ ተሸከርካሪዎች በቀጥታ የግድቡ ቦታ ድረስ በማድረስ ድርጅቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አቶ መስፍን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመጎብኘታቸው ከፍተኛ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው በመግለጽ በቀጣይም ለግድቡ የሚያደርጉት ድጋፍ እንደማይቋረጥና አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡በመጨረሻም በጉብኝቱ ላይ ተሳታፊ ለነበሩ የድርጅቱ የመርከብ ወኪሎች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምስል የያዘ ፈሬም በስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን በጉብኝቱም በሽልማቱም የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል፡፡