የድርጅቱ የመርከብ ወኪሎች ዓመታዊ ጉባዔ ተካሄደ

Body: 

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በዓለም አቀፍ ወደቦች የሚገኙ የድርጅቱ የመርከብ ወኪሎች ዓመታዊ ጉባዔ ከሚያዚያ 18 – 19/2009 ዓ/ም በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡ በጉባዔው ላይ ከ28 አገራት የመጡ 49 የመርከብ ወኪሎች የተገኙ ሲሆን ባለፈው ዓመት የተከናወኑ አበይት ክንውኖችና ያጋጠሙ ችግሮችን በመወያየት ለቀጣይ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ጉባዔ እንደሆነ አቶ መስፍን ተፈራ የድርጅቱ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በጉባዔው መክፈቻ ወቅት ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ መስፍን ተፈራ ገለጻ አገራችን ለተያያዘችው ፈጣን ዕድገት የባሕር ትራንስፖርት ዘርፍ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ እንደሆነ አውስተው በተለይም አገራችን ለምታደርገው የገቢና ወጪ ንግድ መቀላጠፍና መሳካት የድርጅቱ የመርከብ ወኪሎች ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም አገራችን ከፍተኛ መጠን ያለው የገቢና ወጪ ንግድ ልውውጥ እያደረገች እንደሆነ ገልጸው ይህንን ሊሸከም የሚችል ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ድርጅቱ በአገር ውስጥ የሚገኙ ደረቅ ወደቦችን በማስፋፋትና በማልማት ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢና ቀልጣፋ የሎጅስቲክስ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ደረቅ ወደቦችን ከባቡር መስመር ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን የገለጹ ሲሆን የሞጆ ወደብና ተርሚናልን ከአዲስ አበባ - ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር የማገናኘት ሥራዎች እየተጠናቀቀ እንደሚገኝና በቀጣይም የኮምቦልቻንና መቐለ ወደብና ተርሚናልን ከአዋሻ - ወልዲያ - ሃራ ገቢያ የባቡር መስመር ግንባታ ጋር ለማገናኘት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩልም በባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ አገራችን የምትፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችለው የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ ተገንብቶ የተጠናቀቀ መሆኑን አስረድተው በቀጣይ ዓመት በአምስት የተለያዩ ዘርፎች ማለትም Deck, Engine, Engine Service, Freight Forwarding, Port and Terminal ዲፓርትመንቶች ከደረጃ 1-5 ባሉት የቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚሁ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትርና የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው አገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ አገራት ውስጥ አንዷ መሆኗን ገልጸው በዚህም የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ መንግስትም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነና በብሄራዊ ደረጃ የሎጅስቲክስ ስትራቴጅ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

አገራችን ለኢንቨስትመንት የተመቸች እንደሆነችና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ አገር ኢንቨስተሮች መዳረሻ እየሆነች እንደመጣች በጉባዔው ላይ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ ሲሆኑ በተለይም በአገራችን ስላለው ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ለዘርፉ ተዋንያን መንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍና ማበረታቻ ለተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡

ከዚሁ በመቀጠል አቶ እያሱ ይማም የድርጅቱ የመርከብ አገልግሎት ዘርፍ የገቢያና ልማት ዋና ዳይሬክተር በዘርፉ ባለፈው ዓመት ስለነበረው ዋና ዋና የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ወኪሎች ከድርጅቱ ጋር ያከናወኑትን የጭነት ማጓጓዝ (Bill of Loading) ፣ኤች ኤስ ኮድ እና የቲን አጠቃቀሞችን በተመለከተ የሚታዩ ችግሮች ላይ ሰፊ የሆነ ውይይት እና የተሞክሮ ልውውጥ የተደረጉ ሲሆን ጠንካራ ጎኖች ይበልጥ እንዲጎለብቱ እንዲሁም በእጥረት የተነሱት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንደሚገባቸው የጋራ ድምዳሜ በመድረስ ውይይቱን አጠናቅቀዋል፡፡