ድርጅቱ ለተማሪዎች ምገባ የሚውል የ1.1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ስምምት ተፈራረመ

Body: 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ተማሪዎችን ለመመገብ የሚያስችል የ1.1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር ጋር የጋራ ስምምነት ሰነድ መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም ተፈራርሟል.

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ክብርት ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ እንደገለጹት ማህበሩ ከተቋቋመበት 2006 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች የሚማሩ በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ትምህርታቸው ላይ እንዲቆዩና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ በ207 ት/ቤቶች ቁጥራቸው ከ20ሺ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ ከመመገቡ ባሻገር ለ846 እናቶች የስራ እድል በመፍጠር በርካታ እናቶች የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚዎች መሆን እንደቻሉም ክብርት ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የመግባቢያ የስምምነት ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርዓቱ በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በኩል በም/ዋ/ስ/አስፈፃሚ የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ እና በእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር በኩል ደግሞ በማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ በወ/ሮ ድርብወርቅ ልዑልሰገድ አማካኝነት የተፈጸመ ሲሆን በቀጣይም ማህበሩን ለመደገፍ ድርጅቱ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ተፈራ በበኩላቸው ድርጅቱ 450 ተማሪዎችን ለአንድ ዓመት መመገብ የሚያስችል የ1.1 ሚሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነት ማድረጉ እንደ ተቋም ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ህፃናት ተማሪዎችን መደገፍ ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና መሰረት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡